የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በማኅበረሰቡ ጤና አጠባበቅ የጤናና ጤና-ነክ መረጃዎች አዘጋገብና አቀራረብ ዙሪያ ከየካቲት 8-9/2014 ለሁለት ቀናት የቆየ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ለሚዲያና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሰጥቷል፡፡
የሆስፒታሉ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር አብድረሂም በድሩ በስልጠናው ላይ እንደገለፁት በአለምአቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ የሆነውን የኮረና/COVID-19/ ቫይረስ በተመለከተ ትክክለኛና ተገቢ የሆነ መረጃ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ባለመደረጉ እ.ኤ.አ እስከ 2021 መጨረሻ ድረስ ብቻ ከ262 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በቫይረሱ እንደተጠቁ እና ከዚህም ውስጥ ከ5 ሚሊየን በላዩ ለህልፈተ-ህይወት መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም በሚዲያ የሚቀርቡ የጤናና ጤና-ነክ መረጃዎች በህብረተሰቡ ዘንድ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖ ስላላቸው የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች መረጃዎቹን በሚዘግቡበት ወቅት በጥንቃቄ እና ተገቢነት ባለው መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በMedical Journalism እና Health Communication ዙሪያ ስልጠና የሰጡት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የእንግሊዘኛ ቋንቋና ስነ-ፅሁፍ መምህር የሆኑት መምህር ሬድዋን ነጃ የጤና መረጃ ከህብረተሰቡ የዕለት-ተዕለት ህይወቱ ጋር የተያያዘ ስለሆነ በጤናው ዘርፍ የሚዘገቡ መረጃዎች ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ሊሆን እንደሚገባና ህይወትን ለመታደግ ትክክለኛ መረጃ በትክክለኛ ሰዓትና ቦታ ለትክክለኛ አካል መቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ ጤናውን በአግባቡ እንዲጠብቅና በሽታን አስቀድሞ የመከላከል ልምዱን ለማዳበር የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው መምህር ሬድዋን የገለፁ ሲሆን የማህበረሰቡን እውቀትና ግንዛቤ ለማሳደግና የባህርይ ለውጥ እንዲያመጣ ለማድረግ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የጤናም ሆነ የሚዲያ ስራ ያለማህበረሰብ ተሳትፎ ውጤታማ ስለማይሆን ከጤና ጋር በተያያዘ የሚሰሩ የሚዲያ ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር አብሮ የመስራት ልምድ ማዳበር እንደሚያስፈልግ መምህሩ አክለው ገልፀዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ከስልጠናው ትልቅ ግብዓት እንዳገኙበትና በጤና ዘርፍ ላይ የበለጠ ስራ ለመስራት መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው ላይ ከወልቂጤ ኤፍ.ኤም 89.2 ሬዲዮ፣ ከጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች፣ ከጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ፤ ከጉራጌ ዞን የጤና መምሪያ እንዲሁም ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት እና ከዩኒቨርሲቲው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተወጣጡ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡