የምክክር መድረኩን ያስጀመሩት በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ካሳሁን አቤ መድረኩ የግብርናን አስፈላጊነት በጥልቅ ያስገነዝባል ብለዋል፡፡ በሃገሪቱ ዛሬ ላይ የሚታየው የበጋ መስኖ እርሻ ስራ ጥሩ ተስፋ እንደሆነ የተናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ካስሁን ሀገራችን ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ከመጠቀም አንጻር ግን ክፍተቶች እንዳሉ ጠቅሰው ይህንን ለመሙላትም በዘርፉ ያሉ ምሁራን ጥናትና ምርምሮችን በመስራት መፍትሔ ሊያመጡ እና የነገይቱን ኢትዮጵያ ሊገነቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር መቅደስ ደሴ እንደገለጹት የመድረኩ አላማ በሃገር አቀፍ ደረጃ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ እየተሰራበት ያለው የግብርና ስራ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ሲሉ ዩኒቨርሲቲው እንደ ሃገር የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር መቅደስ አያይዘውም ኮሌጁ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በመስራት ላይ ሲሆን የተለያዩ የምርምር ውጤቶችንም ለማህበረሰቡ አበርክቷል ብለዋል፡፡
በእለቱም ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ እንዲሆን የአየር ንብረት ለውጥን፣ ቴክኖሎጂን እና በአሁን ሰዓት ግብርናው ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ተጽእኖ የተመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጽሁፎች በኮሌጁ መምህራን የቀረቡ ሲሆን ሰፊ ምክክርም ተካሂዶባቸዋል፡፡