የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከጉራጌ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር ለስፖርት ሳይንስ ተማሪዎች እና ከዞኑ ለተውጣጡ የስፖርት ባለሞያዎች የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ጀምሯል::
የስልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሃብቴ ዱላ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በተግባራዊ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ምድብ ውስጥ መካተቱን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም በሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ተግባራዊ እውቀት ይዘው እንዲወጡ በሚያደርገው ጥረት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም የዚህ የተግባር ስልጠናም ዓላማ ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር እየቀየሩ ውጤታማ በመሆን በስራው አለም ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን እንዲሁም የዞኑ ስፖርት ባለሞያዎች ተግባራዊ የሆኑ ሳይንሳዊ ስልጠናዎች በመታገዝ የዞኑን ስፖርት የሚያሳድጉበት በመሆኑ አስፈላጊነቱ የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሰልጣኞችም ስልጠናውን በአትኩሮት በመከታተል ተገቢውን እውቀት እንዲገበዩ ዶክተር ሃብቴ አሳስበዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ አደም ሽኩር በበኩላቸው በዞኑ በቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ እና በአትሌቲክሱ ዘርፍ ጉድለት የሚታይባቸው በመሆኑ ስልጠናው ክፍተቶችን በመሙላት የሰው ሃይል ለማሳደግ እንዲሁም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ የሆኑት ዶክተር አብድላዚዝ ሙሰማ ዩኒቨርሲቲው ከዞኑ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ጋር በትብብር እየሰራቸው ያሉትን ስራዎች እንዲሁም ተቋሙ ያደረጋቸው ድጋፎች ላይ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ስልጠናው የንድፈ-ሃሳብ እና የተግባር ሲሆን ለተከታታይ 13 ቀናት እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል፡፡