ሙሉ ወጪው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የተሸፈነው፣ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዘኛ ቋንቋ እና ስነ–ጽሁፍ ትምህርት ክፍል መምህር በሆኑት በመምህር ካሚል ኑረዲን የተጻፈው እና በተለይም በጉራጊና ቋንቋ ሚስጥራት እና ተያያዥ እውነታዎች ላይ ትኩረት ያደረገው “መቅረዝ “ የተሰኘው መጽሀፍ በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቋል ።
የምረቃ ስነስርዓቱ በአባቶች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሀብቴ ዱላ ባስተላለፉት መልዕክት መምህር ካሚል ኑረዲንን አመስግነው መጽሀፉ ለዚህ እንዲበቃ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት እገዛ ማድረጉን በመግለፅ በቀጣይም የጉራጊና ቋንቋን በማሳደግ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ክቡር አቶ ደግነህ ቦጋለ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የመፅሀፉን ደራሲ መምህር ካሚልን አመስግነው በክልሉ ውስጥ ያሉትን ቋንቋዎች እና ባህሎችን በማሳደግ ረገድ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
“መቅረዝ “ መጽሃፍ ለሰው ልጅ ትልቁ ጸጋ የሆነውን የቋንቋን ሁለንተናዊ ጉዳይ በስፋት እንደሚዳስስ፣ በተለይም የጉራጊናን ቋንቋ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማመላከት ረገድ ሰፊ ድርሻ እንዳለው በፕሮግራሙ ላይ መጻፉን በዳሰሳ ያቀረቡት ዶክተር ፈቀደ ምኑታ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ ዶክተር ጌታቸው ደዊ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር የታሪክ፣ የቋንቋ እና የባህል መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር መዘምር ተክለአብ ሰፊ ዳሰሳቸውን አቅርበዋል፡፡
መምህር ካሚል ኑረዲንም በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተደረገላቸው እገዛ መጽሀፉ ለህትመት በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው በተለያየ መልክ ድጋፍ ያደረጉትን አካላት በሙሉ አመስግነዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት አባላት፣ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የካውንስል አባላት፣ የተከበሩ ወይዘሮ ልክነሽ ስርገማ የጉራጌ ዞን ዋና አፈጉባዔ፣ ክብርት ወይዘሮ መሰረት አመርጋ የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ ቅባቱ ተሰማ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር (ጉልባማ) ዋና ዳይሬክተር ፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች፣ ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ልዩ ልዩ እንግዶች የተገኙ ሲሆን ለመድረኩ ድምቀት በመሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ በዩኒቨርሲቲው የሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ግጥሞች እና መነባነብ ቀርቧል።
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት