የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ባዘጋጀው የመስክ ጉብኝት ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ተመራማሪ የሆኑት መምህር አስራት ፍቅሬና የደንና አየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪ የሆኑት መምህር ሰለሞን አብርደው ስለ ችግኞች ኣዘገጃጀት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተደረገው የመስክ ጉብኝት በችግ|ኝ ጣቢያው 12 አይነት ዝርያ ያላቸው ብዛታቸው ከ105000 (አንድ መቶ አምስት ሺህ ) በላይ የሆኑ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸው እነዚህም ችግኞች በሶስት አይነት ደረጃ ተከፋፍለው መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል ፡፡ አንደኛው የአካባቢ ውበትና ስነ ምህዳር ለመቀየር፣ ሁለተኛው በተፈጥሮ ክስተት የተጎዱ አፈርና ውሀ እንዲያገግሙ ለማድረግ እና ሶስተኛው ለመድሀኒትነት የሚውሉ ችግኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ አመት ለመትከል የተዘጋጁ ችግኞች ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ ጥራታቸው የተጠበቀና በፖት የተዘጋጁ መሆናቸውን ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ችግኞቹን ለመትከል በቂ ዝግጅት የተደረገ መሆኑን በመግለፅ ችግኞቹም በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ፣በስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዙሪያ እና በዞኑ በሚገኙ የከተማ መስተዳድሮች ለመትከል መታቀዱን ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም በኦሞ ግቤ ተፋሰስ 15000 በስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ 5000 እንዲሁም በተለያዩ የዕምነት ተቋማት ጭምር እንደሚተከልም ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡