በዩኒቨርስቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና በዩኒቨርሲቲው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚሰጠው ይህ የትምህርት ፕሮግራም 12 የህክምና ዶክተሮችን የተቀበለ ሲሆን በቀዶ ህክምና እና በወሊድና ማህፀን ሕክምና የስፔሻሊቲ ትምህርት ለመስጠት ነው።
የስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ ቺፍ ኤክስከቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር አብድረሂም በድሩ በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የሚጀምሩት ሁለት ፕሮግራሞች ለተቋሙ ብሎም ለአካባቢው ማህበረሰብ ያለው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሆስፒታሉ ከተጀመረ ሶስት አመት እንዳልሆነው የገለፁት ዶክተር አብድረሒም እስካሁን ድረስም ከ130ሺህ በላይ ሰወች የህክምና ግልጋሎት አግኝተዋል ብለዋል። ይሁን እንጂ ከታካሚዎቹ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በስፋት ከሚስተዋሉ የጤና ችግሮች የማህፀንና ፅንስ እንዲሁም የቀዶ ህክምና በመሆናቸው ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት የማህበረሰቡን የህክምና እጦት ለመቅረፍ በቀዶ ህክምና እና በወሊድ እና ማህፀን ሕክምና የስፔሻሊቲ ትምህርት ለመስጠት እና በሆስፒታሉ እንዲያገለግሉ በማሰብ ከጤና ሚኒስቴር 12 ዶክተሮችን ተቀብሏል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሆስፒታሉ በተለያዩ የህክምና ዘርፎች 32 ስፔሻሊስት ዶክተሮች በማገልገል ላይ መሆናቸውንም ዶክተር አብድረሒም ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ረቢ አሊ ሆስፒታሉ በአራት ዋና ዋና የህክምና ዘርፎች ህዝቡን እያገለገለ ይገኛል በማለት የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎችን በማሟላትም የታካሚውን እንግልት ለመቀነስ እየጣረ ነው ያሉት ዶ/ር ረቢ ለዚህም በቅርቡ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጣው የሲቲ እስካን ማሽን ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ረቢ አያይዘውም ዛሬ ወደ ተቋሙ የተቀላቀሉ ሪዚደንቶችም በሚኖራቸው የትምህርት ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ተክለሚካኤል ገብሩ በበኩላቸው የስፔሻሊቲ ሰርትፊኬት በቀዶ ህክምና እና የወሊድ እና ማህፀን ሕክምና ፕሮግራሞች መጀመር የዩኒቨርሲቲውን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶችን ከማስጀመርና የአገልግሎቱ ጥራት ከማሻሻል ባሻገር የህብረተሰቡን የህክምና ፍላጎት በሟሟላት ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡