በስልጠናው ላይ የተሳተፉት መካከለኛ አመራሮች የተውጣጡት ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፤ከዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፤ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ፤ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፤ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፤ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፤ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እና ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በመክፈቻ ንግግራቸው ባስተላለፉት መልዕክት ስልጠናው የመካከለኛ አመራሮችን የመፈጸም አቅም የሚያጎለብትና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸው ከስምንቱም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡት መካከለኛ አመራሮች የተሻለ ልምድ የሚለዋወጡበትን አጋጣሚ ስልጠናው እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም መካከለኛ አመራሩ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች በመለየትና መፍትሔ በመስጠት የትምህርት ጥራትና አግባብነት የማረጋገጥ ሥራን በውጤታማነት መምራት እንደሚጠበቅበት፤ የትምህርት ስራው ውጤት የትምህርት አመራሩ ነፀብራቅ መሆኑንና መካከለኛ አመራሩ የትምህርት ባለድርሻ አካላትን በሚገባ አደራጅቶ፤ ጠንካራ የአፈጻጸም ስርዓት ገንብቶ የሚመራ ከሆነ የተሻሉ ውጤቶች እንደሚመዘገቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል ፡፡ ስልጠናውን የሚሰጡት ከትምህርት ሚኒስቴር የመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ሲሆኑ ስልጠናው እስከ ታህሳስ 17/2014 ዓም ድረስ የሚቆይ መሆኑን ከስልጠናው አስተባባሪዎች ለመረዳት ችለናል፡፡