በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና በዞኑ ትምህርት መምሪያ ትብብር በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት (ቱቶሪያል) የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ተማሪዎችና ወላጆች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል ገለጹ።ዶክተር ፋሪስ ደሊል ይህንን የገለጹት በጉራጌ ዞን በተለያዩ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህርት (ቱቶሪያል) እየተሰጣቸው ያሉትን ተማሪዎችን በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡
ዶክተር ፋሪስ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት ተማሪዎች ይህንን የተፈጠረላቸውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲጥሩ፣ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርት እንዲያውሉ፣ ለትምህርት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡና ነገን ተስፋ አድርግው በርትተው እንዲማሩ ልምዳቸውንም ጭምር በማካፈል የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።
ዶክተር ፋሪስ አያይዘውም ለተማሪዎች ውጤታማነት የወላጆች ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸው ወላጆች ልጆቻቸውን በመቆጣጠር በመልካም ስነ ምግባር እንዲታነጹ በማድረግ በተለይም ወቅታዊ ውጤታቸውን በቅርበት እንዲከታተሉ አሳስበዋል ።
ዩኒቨርሲቲው በጉራጌ ዞን፣ በምስራቅ ጉራጌ ዞን፣ በየም ዞንና በቀቤና ልዩ ወረዳ በተመረጡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ የሆኑ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ዶክተር ፋሪስ ገልጸው በቀጣይ ዩኒቨርስቲው ያለውን የሰው ሀይልና ዕውቀት ተጠቅሞ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በሁሉም አካባቢዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለትምህርት ውጤት መሻሻል እንዲሁም የትምህርት መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድ መንግስትና ማህበረሰቡ እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ በትኩረት ከመደገፍ አንጻር ዩኒቨርሲቲው የበኩልን ድርሻ እንደሚወጣ ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማርያም በበኩላቸው እንደገለጹት የማጠናከሪያ ትምህርት (የቱቶሪያል እገዛው) ከመጀመሩ በፊት በፕሮግራሙ ለሚካፈሉት መምህራኖች ስልጠና መሰጠቱንና አስፈላጊ የሆነ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስታውሰው ቱቶሪያሉ መምህራኖች ያላቸውን ዕውቀትና ልምድ ለተማሪዎች የሚያስተላልፉበት አጋጣሚ በመሆኑ የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል ።
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት