ፕሮግራሙ በአባቶች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ዮሃንስ ገብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ዓባይ ድህነትን ማሸነፍ እንደምንችል ዳግም ትምህርት የሰጠን፣ግንድ ይዞ ሳይሆን ሀይል ይዞ የሚጓዝ የኢትዮጵያ ተስፋ፣ ጠላቶቻችን “ አይችሉም ፣አያሳኩም” በማለት የተዘባበቱብንን ከንቱ ሀሳብ ድል ያደረገና በራሳችን ሁሉ አቀፍ አቅም መገንባት መቻላችንን በተግባር ያስመሰከርንበትና አሁን ላይ ግንባታውን 95% ማድረስ የቻልንበት፤ የይቻላል መንፈስን ያጠናከረ እና የህብረ-ብሄር አንድነት መሰረት እንዲሁም የአንድነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ከቀረቡት ዝግጅቶች መካከል አባይ ተኮር ግጥሞችና ዘፈኖች ያላቸውን ፋይዳ በተመለከተ አጭር ቅኝት በመ/ር ወርቁ ሙሉነህ (ረ/ፕ/ር) አማካይነት ሰፊ ዳሰሳ ያዘለ ቅኝት በዝርዝር ቀርቧል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ልዩ ልዩ ግጥሞች በዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች ከመቅረባቸው ባሻገር ኢትዮጵያ ዓባይን ለልማት ከመጠቀም አንጻር ከዓለም አቀፍ ህግ አኳያ ያላትን መብት አስመልክቶ ሰፊ የሆነ ሙያዊ ትንታኔ በህግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቀርቧል፡፡
በመጨረሻም ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ከተሰጠ በኋላ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ተጠናቅቋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎች ታድመዋል፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት