በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው “የተሽከርካሪ አያያዝና አጠቃቀም የውስጥ አሰራር ስርዓት መመሪያ” ዙሪያ ለወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አሽከርካሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ኮርፖሬት ማኔጅመንት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር የሺሀረግ አፈራ ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደገለጹት መመሪያውን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያት፡-
- በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የተሽከርካሪዎች ስምሪትና አጠቃቀም አሰራር ውስጥ ያልተሸፈኑ ዝርዝር ጉዳዮች በሕግ ማዕቀፍ እንዲሸፈኑ በማድረግ መመሪያዉ በተሻለ ሁኔታ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችልበት ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ፣
- ከተሽከርካሪ አያያዝና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲው ሊያጋጥመዉ የሚችለዉን አላስፈላጊ ወጪን ለመከላከል የሚያስችል ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሥርዓትን መዘርጋት በማስፈለጉ፣
- ከተሸከርካሪ አጠቃቀምና አያያዝ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የስነ ምግባር ችግሮችን ለመከላከል የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ይህንን የተሽከርካሪ አያያዝና አጠቃቀም የውስጥ አሰራር ስርዓት መመሪያ ማዘጋጀቱንና በመመሪያው ዙሪያ ዋና ፈጻሚ ለሆኑት አሽከርካሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
መመሪያው ለአሽከርካሪዎቹ በዝርዝር የቀረበ ሲሆን መመሪያውን መሰረት በማድረግ ከአሽከርካሪዎች ለተነሱት ጥያቄዎች በአስተዳደርና ኮርፖሬት ማኔጅመንት ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ደረጃ ምላሽ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች በዕለቱ ምላሽ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን በአንጻሩ በዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ደረጃ ምላሽ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች በተዋረድ ለማኔጅመንቱ ቀርበው ምላሽ እንደሚሰጥባቸው በዕለቱ ተገልጿል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው የተሽከርካሪ አያያዝን ለማዘመንና ወጪ ቆጣቢ የሆነ አሰራር ለመዘርጋት ለ24 ተሽከርካሪዎች ጂፒኤስ በማስገጠም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን የዚህን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም አስመልክቶ ያለውን አጠቃላይ መሻሻል ለመገምገም የተሞከረ ሲሆን ለተሸከርካሪዎቹ ጂፒኤስ በማስገጠም አገልግሎት መሥጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለነዳጅ በተጨማሪነት ሲወጣ የነበረ ብር 573,000 (አምስት መቶ ሰባ ሶስት ሺህ ብር) ለማዳን መቻሉ ተገልጿል፡፡ ይህ ከጅምሩ የሚበረታታ ተግባር እየተመዘገበበት ያለውን የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ በዕለቱ ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም አሽከርካሪዎች ለተገልጋዮች አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት አልፎ አልፎ በተወሰኑ አሽከርካሪዎች ዘንድ በሚስተዋሉት የስነምግባር ችግሮች ዙሪያ በስፋት ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ተችሏል፡፡