ስልጠናውን በንግግር ያስጀመሩት የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር እና ኮርፖሬት ማኔጅመንት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር የሺሀረግ አፈራ ባስተላለፉት መልዕክት የስልጠናው ዋና ዓላማ በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሃላፊነት እርከን ላይ የሚገኙ የመካከለኛና እና የመሰረታዊ አመራሮች በመንግስት አስተዳደራዊ መመሪያዎች ማለትም በሰው ሀብት አስተዳደር መመሪያ፣ በፋይናንስ አስተዳደር መመሪያ፣ በግዢና ንብረት አስተዳደር መመሪያ ዙሪያ በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማስቻል፣ ንብረትን በአግባቡና ህጉ በሚፈቅደው መሰረት የማስተዳደር ሃላፊነት እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ ለማድረግ እንዲሁም በተለይም አዳዲስ አመራሮች ወደ ሃላፊነት ሲመጡ መመሪያውን አውቀው እና ተከትለው በመስራት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ሰፊ የሆነ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንዲረዳ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶክተር የሻረግ አፈራ አያይዘውም የግዥ ስርዓቱን በተመለከተ ተቋሙ አሁን ላይ ትክክለኛ አሰራርን በመከተል በተሻለ አፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው የተቋሙ የ2014 ዓ.ም.የኦዲት ምርመራ አስተያየት Except For በሚባል አበረታች ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው በያዝነው የበጀት አመት ከኦዲት ግኝት ነጻ የሆነ ተቋም ለመፍጠር ሁሉም የባለድርሻ አካላት የአሰራር ጥሰቶችን በመከላከል በግዥ እና ንብረት አስተዳደር መመሪያ መሰረት መፈጸም እንደሚገባቸውም ጭምር አሳስበዋል፡፡
ስልጠናውም ከፌዴራል ግዥ እና ንብረት አስተዳደር በመጡት በአቶ ዘነበ ሰመሩ አማካኝነት የተሰጠ ሲሆን የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ዘዴ እንዲሁም የግዥ እና ንብረት አስተዳደር መመሪያ በተመለከተ ሰፋ ያለ ትንታኔ የቀረበ ከመሆኑም በላይ በዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በኩል የፋይናንስ ደንብ እና መመሪያ እንዲሁም በሰው ሃብት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በኩል የሰው ሃብት ደንብ እና መመሪያ ለሰልጣኞቹ በዝርዝር ቀርቧል፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት