Research Methodology and Statistical Software (SPSS, STATA, R, SAS, & ODK) በሚል ርዕስ የስታትስቲካል ማማከር እና ትብብር ማዕከል ከምርምር ዳይሬክቶሬት ጋር በጋራ በመቀናጀት ያዘጋጁት ስልጠና ለመምህራን በመሰጠት ላይ ነው ፡፡
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ዮሀንስ ገብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ሲሰራ እና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው እነዚህ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎቶች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ ለማስቻል በሁለት አበይት ጉዳዮች ላይ ማለትም ተግባራዊ እና ችግር ፈቺ ምርምሮችን በመስራት እና በማሰራጨት እንዲሁም የተለያዩ አደረጃጀቶችን በማጠናከር እና ልዩ ልዩ የአሰራር መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ተግባር የመግባት ስራዎች ላይ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ዮሀንስ በዩኒቨርሲቲው ደረጃ በዋነኝነት የተከናወኑትን ዋና ዋና ተግባራትን ሲገልጹ የምርምር ፡ የማህበረሰብ አገልግሎት እና የጆርናል ኤድቶሪያል ፖሊሲ በሴኔት መጽደቁን፣ የውስጥ አሰራር ን ለማዘመን የሚያግዘውን IRMS በማሻሻል ወደ ተግባር መገባቱን፣በምርምር ሳይቶች ላይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች የተሻለ ውጤታማ እንዲሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መጨመራቸውን፣ የባለድርሻ አካላትን ትብብር እና አጋርነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ እንዲያግዝ የማህበረሰብ አገልግሎት ቀንን ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን እና የመምህራንን አቅም የሚያሳድጉ ልዩ ልዩ ስልጠናዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው የዛሬውም ስልጠና የዚሁ አንዱ አካል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዶክተር ዮሃንስ አያይዘውም ሲገልጹ ስልጠናው የተሳታፊዎችን ምርምር የመስራት አቅም ከማሳደግ አንጻር የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል ፡፡
ስልጠናው ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ከወጣው የድርጊት መርሀ-ግብር ለማወቅ ችለናል፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙት ዳይሬክቶሬት