የእውቅና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል ባስተላለፉት መልዕክት ለተመዘገበው ውጤት መሳካት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ፣ለተሻለ ውጤት መምጣት ሌት ተቀን ለፍታችሁ አስደሳች የሆነ ውጤት እንዲመዘገብ ላደረጋችሁ ሁሉ ፣ዛሬ ላይ በኩራት ይህንን ውጤት ለመዘከር ላበቃችሁን ለሁሉም የባለድርሻ አካላት በሙሉ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የሀገራችንን የትምህርት ጥራት ስብራት ለመጠገን መንግስት ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎችን እየተገበረ መሆኑን ዶክተር ፋሪስ ገልጸው ለዓመታት የነበረው የምዘና ስርዓታችንን ለማስተካከል፣ ተማሪዎች ከኩረጃ በጸዳ ሁኔታ በራስ የመተማመን ብቃታቸውን በመጨመር ፣በየተቋማቱ የሚታየውን የምዘና ወጥነት ለማስተካከል እና በሀገራዊ ስታንዳርድ መመዘኛ መሰረት ተማሪዎችን ለማብቃት የመውጫ ፈተና መዘጋጀቱን ዶክተር ፋሪስ ገልጸዋል፡፡
ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲም የጤና ሳይንስ ኮሌጅን ሳይጨምር በ43 ፕሮግራሞች በመደበኛ ፕሮግራም ካስፈተናቸው ተማሪዎች 79.6 በመቶ ማሳለፍ መቻሉን ዶክተር ፋሪስ ገልጸው ውጤቱ ከሀገራዊ አማካዩ ማለትም ከ62.3 በመቶ አንጻር እና ከበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሲነጻጸር የላቀና እጅግ ተስፋ ሰጪ ውጤት መሆኑን ገልጸው በዚህ ውጤት ያኮራችሁን የቀድሞ ተማሪዎች፣ ለውጤቱ መሳካት ሙሉ አቅማችሁን የተጠቀማችሁ መምህራን እና በሁሉም እርከን ያላችሁ የዩኒቨርቲያችን አመራሮች እና የተቋሙ የቀድሞ አመራሮች ጭምር ልፋታችሁ ፍሬ ስላፈራ ልትኮሩ ይገባል በማለት የሞቀ ደስታቸውን ገልጸዋል ፡፡
ዶክተር ፋሪስ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች በጥሩ ውጤት ያስመረቅናቸውን እንቁ ተማሪዎችን ወኔ ሰንቀው እነሱን እንደተምሳሌት በመውሰድ ለአፍታም ሳይዘናጉ ሁሌም በማጥናት ዳግም በልፋታቸው ኮርተው ዩኒቨርሲቲውን እንዲያኮሩ ፣ መምህራንም በዘንድሮው ዓመት ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተግተው እንዲሰሩ፣ በየደረጃው ያለው አመራሩም ዛሬም ነገም የአመራር ጥበቡን ፣ ጥረትና ጥንካሬውን እንዲያስቀጥል አደራቸውን ገልጸዋል፡፡
ከዶክተር ፋሪስ የመክፈቻ ንግግር በኋላ በ2015 ዓ.ም. በሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አፈጻጸም የጥናት ውጤት በዝርዝር ቀርቦ በቀረበው ጥናት ዙሪያ የተለያዩ ጠቃሚ ሀሳቦች ተነስተው የጋራ ውይይት ተደርጎበታል ፡፡
በተመዘገበው አጠቃላይ አፈጻጸም ካሉት ኮሌጆች መካከል ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ፡-
1ኛ) የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ
2ኛ) የማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ
3ኛ ) የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በመጨረሻም ከፍተኛ የሆነ ውጤት ላስመዘገቡ ኮሌጆች እና የትምህርት ክፍሎች ሽልማት እና የምስክር ወረቀት ከመሰጠቱም በላይ ለዚህ ውጤት ከፍተኛውን ድርሻ ለሚወስደው ለዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንትም እውቅና ተሰጥቷል፡፡
የመውጫ ፈተና (Exit Exam) ብቁ የሰው ሃይል በማዘጋጀት ወደ ኢኮኖሚ መግባቱን ማረጋገጫው አንደኛው መንገድ ሲሆን ተመራቂዎች በተማሩበት ሙያ ዘመኑ የሚጠይቀውን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ገንብተው ስለመውጣታቸው የሚመዝን ከመሆኑም ባሻገር ዲግሪ በያዙ ተመራቂዎች መካከል በብቃት የሙያውን ምሉዕነት ተላብሶ የተመረቀው የትኛው እንደሆነ ለመመዘን የሚያስችል ከጥራት ማረጋገጫ መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት