የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ በተለይም በአበሽጌ ወረዳ በሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ፣በዘርፉ በተሰማሩ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች እና በማህበረሰቡ ተወካዮች ዘንድ ተገቢውን ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ ነው፡፡ በተጨማሪም በህመሙ ዙሪያ ዕውቀትን መሰረት ያደረገ የሃሳብ ልውውጥና የምክክር መድረክ በማድረግ ለማህበረሰቡ የጉዳዩን አሳሳቢነት እና ያሉትን ተግዳሮቶች ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ እንደሆነ የውይይት መድረኩን ካዘጋጁት ክፍሎች ለማወቅ ተችሏል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት ከአበሽጌ ወረዳ የተውጣጡ የስነ-አዕምሮ ሀኪሞች፣ ዋና ዋና ፈጻሚዎች፣የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች፣ነርሶች፣በልዩ ልዩ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ሰራተኞች እና የማህበረሰብ መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉት የባለድርሻ አካላት በአዕምሮ ጤና እክሎች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ እና አጠቃላይ እይታ አስመልከቶ ያላቸውን ግንዛቤ በመድረኩ ላይ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የታወቁ የአዕምሮ ህመም ዓይነቶች ፣ምልክቶቹ እንዲሁም በግለሰብም ሆነ በማህበረሰብ ደረጃ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ፣ ህመሙን እንዴት መለየት እንደሚቻል፣ ህመሙን ከጅምሩ መፍትሄ ለመስጠት ስለሚወሰደው አፋጣኝ እርምጃ አወሳሰድ ስልቶች እንዲሁም ህሙማኑን ከማግለል ይልቅ እንዴት አቅርበናቸው ተገቢውን የስነልቡና ድጋፍ መስጠት እና ወደጤንነታቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚቻል አስመልክቶ ሰፊ የሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመድረኩ የተለያዩ የዳሰሳ ጥናቶች የቀረቡ ከመሆናቸውም በላይ ማህበረሰብን ያማከለ የአዕምሮ ጤና ድጋፍ ማድረግን አስመልክቶ ሰፊ የሆነ እና ጠቃሚ ምክክር ተደርጓል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በቡድን ሆነው የአዕምሮ ጤና ዕክል ከባህል አንጻር ያለውን እይታና የማህበረሰቡ መሪዎች ችግሩን በዘላቂነት ከመፍታትና ተገቢውን ድጋፍ ከማድረግ አንጻር ያላቸውን ሚና አስመልክቶ ጠቃሚ የሆነ ውይይት አድርገዋል፡፡
የዚህ ውይይት መድረክ ዋነኛ ተጠቃሚ የሚሆኑት በተለይም በአዕምሮ ጤና ዙሪያ በብዛት ወገኖቻቸው ተጠቂ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት የጤና ባለሙያዎችና የማህበረሰብ መሪዎች ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት በመጨበጥ ከምክክር መድረኩ በኋላ ወደማህበረሰባቸው ሲመለሱ ለችግሩ ተጠቂ ለሆኑት አካላት ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ለችግሩ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ያመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከውይይት መድረኩ በሚገኘው ግንዛቤ መሰረት የውይይቱ ተሳታፊዎች ወደማህበረሰባቸው ሲመለሱ የህመሙ ተጠቂዎችን ከማግለል ይልቅ የማህበረሰቡ አንዱ አካል መሆናቸውን በመገንዘብ ለተሻለ ጤንነት በዘላቂነት ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የአዕምሮ ጤና ማለት አንድ ሰው ያለውን አቅም ለመጠቀም፣ በዕለት ተዕለት ኑሮው የሚያጋጥመውን ውጥረት ለመቋቋም እንዲሁም በሚኖርበት ማህበረሰብ ፍሬያማ አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚያስችለው የስነ-ልቦና ሁኔታ ላይ መሆን ማለት እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ የስነ-ልቦና ሁኔታ ከተለመደው መስተጋብር ውጪ የሆኑ በአዕምሮ ላይ በሚፈጠሩ ጫናዎች ማለትም ባልተስተካከለ የትምህርት ወይም የስራ ሁኔታ፣ በቤተሰብ ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ብሎም በእርስ በርስ ግንኙነቶች ላይ በሚኖሩ ውጥረቶች ሊረበሽ እንደሚችልም አያይዘው ያስረዳሉ፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት