ዩኒቨርሲቲው የ2016 ዓ.ም የክረምት የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩን በእንደጋኝ ወረዳ በቻ ቀበሌ 1200 (አንድ ሺ ሁለት መቶ) ችግኞችን በመትከል ጀምሯል
በዘንድሮው አመት ለመተከል ከተዘጋጁት 105,000 (አንድ መቶ አምስት ሺህ ) ችግኞች ለምግብነትና ለመድሀኒትነት የሚያገለግሉ አምስት አይነት የሀገር በቀል እንዲሁም ስድስት አይነት የውጭ ዝርያዎች በድምሩ 11 የተለያዩ ዝርያ ያላቸው የዛፍ ችግኞች ተዘጋጅተዋል።
የችግኝ ተከላ መረሀግብሩ ላይ ተገኝተው "የዛፍ ፍይዳው ሰፊ ነው" ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል ምቹና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር ሁሉም ዜጋ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የራሱን አሻራ በማኖር ''የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ'' መርህን ለመተግበር የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም ፕሬዝዳንቱ ወረዳው ላደረገው አቀባበል አመስግነው ባለፈው አመት በዚሁ ቀበሌ የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ ላደረጉት ድጋፍ፣ ክትትል እና እንክብካቤ ለእንደጋኝ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት እና ለአካባቢው ማህበረሰብ ልባዊ ምስጋና በመቸር ዛሬ የተተከሉትንም በተመሳሳይ ትኩረት በመስጠት እንዲንከባከቡ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል።
ዛሬ በተካሄደው የችግኝ ተከላም የዩኒቨርሲቲውን ማኔጅመንት አባላት ጨምሮ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ተማሪዎች እና የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን የበጎ ፍቃድ ተማሪዎችም ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን የጉራጌን ማህበረሰብ አኗኗር እንዲሁም ቅን የሆነ የእንግዳ አቀባበልና ባህላዊ የመስተንግዶ ስርዓቱ ከብዙ በጥቂቱ ለማየት ችለዋል።
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት