ዩነቨርሲቲው የተግባራዊ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ከመሆኑ አንጻር በሚሰጣቸው የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲሁም በሚያከናውናቸው የምርምር አጀንዳዎች የኢኮኖሚውን ውጤታማነት ለማሳደግ በተቀናጀ ሁኔታ ከተለያዩ የኢንደስትሪ ተቋማት ጋር በትስስር መሥራት ስለሚጠበቅበት ለዚህ ተግባር የሚያግዘውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ከተለያዩ የክልል ቢሮዎች፣ ከዞን መምሪያዎችና ከአምራች የኢንደስትሪ ተቋማት ጋር ተፈራርሟል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል ባስተላለፉት መልዕክት የተዘጋጀው የምክክርና የመግባቢያ ስምምነት የመፈራረሚያ መድረክ በዩኒቨርሲቲው፣ በምርምር ተቋማት እና በኢንዱስትሪ መካከል አጋርነትንና ትብብርን ለማሳደግ፣የቴክኖሎጂ ፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ፣ የትምህርትና የምርምር ጥራትን ለማሻሻል፣ ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችን ባገናዘበ መልኩ በቅንጅት፣ በወጥነት፣ በውጤታማነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ ለመስራት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የኢንደስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዴስክ ሃላፊ የተከበሩ አቶ ተሾመ ዳንኤል የከፍተኛ ትምህርት ፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንደስትሪ ትስስር አዋጅ ቁጥር 1298/2023 አስመልክቶ ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ባቀረቡት ዝርዝር ማብራሪያ መነሻነት ከምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የሳይንስ፣ ኢንፎርሜሽና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት የተከበሩ አቶ ሰላሙ አማዶ በበኩላቸው በተነሱት አስተያየቶች ላይ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በቀጣይ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ አብረው ለመስራት ፍላጎታቸውን ካሳዩ የክልል ቢሮዎች፣ የዞን መምሪያዎች፣የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና ኢንደስትሪዎች ጋር በጋራ አብሮ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ዩኒቨርሲቲው የተፈራረመ ሲሆን የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች የምግብ ምህንድስና ላቦራቶሪን ጎብኝተዋል፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት