(ጳጉሜን1/2015ዓ.ም የወ/ዩ/የህ/ዓ/ግ/ዳ/ት) ፡- በጉራጌ ዞን ከሚገኙ ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ካሉት ተማሪዎች መካከል ተውጣጥተው በክረምቱ መርሀ ግብር በሳይንስ ፣ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስናና ሂሳብ (STEM) ፕሮግራም ላይ በሳይንስ ላብራቶሪ 180 በፈጠራ ስራ 30 በድምሩ 210 ጎበዝ ተማሪዎች ስልጠናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በዛሬው ዕለት አጠናቀቁ፡፡
በስልጠናው መዝጊያ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አግልግሎት ዳይሬክተር ቸርነት ዘርጋ (ረ/ፕ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ተማሪዎች በቆይታቸው በጽንሰ ሀሳብና በተግባር የታገዘ ትምህርት ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልጸው ስልጠናው በአብዛኛው በቤተሙከራ የተደገፈ ፣ በተግባራዊ ትምህርት የታገዝ ፣ተማሪዎች ተገቢውን ዕውቀት እና ክህሎት እንዲጨብጡ በማድረግ ረገድ ላይ ትኩረት ያደረገ እና የተማሪዎችን የፈጠራ ችሎታ የሚያዳብር ስልጠና እንደነበር ገልጸው ለበለጠ ውጤት እንዲተጉ የሚያደርጋቸው ስልጠና እንዳገኙ አቶ ቸርነት ዘርጋ (ረ/ፕ/ር) አብራርተዋል፡፡
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው ሰፊ የሆነውን የህይወት ልምድና ተሞከሮአቸውን በስፋት ለተማሪዎቹ ያካፈሏቸው ሲሆን አያይዘውም ሀገራችን ድሀ ብትሆንም በተፈጥሮ ጸጋ የታደለች ነችና ይህንን ችሮታ ወደሀብት በመለወጥ፣ አንገታችንን ያስደፋንን ድህነትን በማሸነፍ፣የሚገጥሙንን የህይወት ፈተናዎችን በጽናት በመሻገር፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም የስልጣኔ ምልክት መሆኑን በውል በመገንዘብ፣ቤተሰብን በማገዝ ፣ የማንበብ ባህልን በማዳበር ለወላጅም ሆነ ለሀገር የቀጣይ ተስፋ እንዲሆኑ በማለት የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ተማሪዎች ስለቆይታቸው የተሰማቸውን ስሜት የገለጹ ሲሆን በቆይታቸው በትምህርትና በፈጠራ ስራዎች ላይ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡት ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት