ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የትምህርት ክፍል (ዲፓርትመንት) ምርጫ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ተሰጠ
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የአንደኛ መንፈቅ ዓመት መጠናቀቁን ተከትሎ ምርጫቸውን በጤናው ዘርፍ ለማድረግ ለሚፈልጉ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች እንዲሁም የህግ ትምህርት ክፍልን መምረጥ ለሚፈልጉ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በቀጣይ ያስመዘገቡትን ውጤት መሰረት አድርገው እንደየፍላጎታቸው መምረጥ የሚገባቸውን የትምህርት መስክ ለመምረጥ የሚያግዛቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ተሰጥቷል።
በመድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራር ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ዮናታን ሙሉሸዋ እንደገለጹት ተማሪዎች ባስመዘገቡት ውጤት መሠረት በቀጣይ በምርጫቸው መማር የሚፈልጉትን የትምህርት ክፍል በራሳቸው መርጠው ለመማር መወሰናቸው ወደፊት ተመርቀው በሚሰማሩበት የስራ መስክ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው በመግለጽ በየትምህርት ክፍሉ የሚሰጠውን አጠቃላይ የሆነ ገለጻ በአግባቡ በማዳመጥ ዝንባሌያቸውን መሰረት ያደረገ ምርጫ እንዲመርጡ አሳስበዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ በህግ ትምህርት ቤት ዲን በመምህር ቀኙ ሙሉ እንዲሁም በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከተለያዩ የትምህርት ክፍሎች በተውጣጡ የስራ ሃላፊዎች አማካይነት ለተማሪዎቹ ሰፊ የሆነ ገለጻ ተሰጥቷቸዋል ።