በሴሚናሩ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲያችን የማኔጅመንት አባላት፣ የካውንስል አባላት፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል ባስተላለፉት መልዕክት የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቁ፣ለፈጣን ዕድገት ምቹ መደላድልን የሚፈጥሩ ሀገራዊ አጀንዳዎች በነጻ ውይይት በማዳበር እና በህዝባችን ዘንድ በማስረጽ ረገድ ሁሉም ዜጋ ሀገራዊ የሞራል ግዴታውን እንዲወጣ ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ፋሪስ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲዎች የሀገራችን ምሁራን መፍለቂያ ማዕከል እንደመሆናቸው መጠን ለሀገራችን ብሎም ለመሪዎቻችን ግብዓት የሚሆኑ በሳልና በጥናት የተደገፉ ሀሳቦችን በማቅረብ ፣ የሀገራዊ ጥቅሞችን ሊያስከብሩ የሚችሉ አስተሳሰቦችን በህዝባችን ዘንድ በማስረጽ፣ በህብረተሰባችን ዘንድ የጋራ መግባባትን በመፍጠር እና ለትግበራው ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በማድረግ ረገድ የተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ፋሪስ አክለውም ለዘመናት የህዝባችን ጥያቄ የሆነውና በተለይም ከኤርትራ መገንጠል ማግስት ጀምሮ ምላሽ ያላገኘው የባህር በር (የወደብ) ጥያቄን ፍጹም ሰላማዊና ዓለም አቀፍ ህጎችን መሰረት ባደረገ መልኩ ለመፍታት መንግስት ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውሰው የባህር በር ጉዳይ የመንግስት ሀሳብ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጉዳይ እንደሆነ በመገንዘብ የባህር በር እንዴት ? ከየት? መቼ? ወዘተ.. በሚሉ ሃሳቦች ላይ ምክክር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑን ገልጸው ይህ መድረክ መዘጋጀቱን ዶክተር ፋሪስ ደሊል በንግግራቸው ላይ አብራርተዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የምሁራንን እይታ መሰረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሁፎች በዘርፉ ባለሙያዎች አማካይነት ለተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ትኩረት የተደረገባቸው ዋና ዋና ነጥቦች ፡-
v ኢትዮጵያና የባህር በር ታሪካዊ ዳራ
v የባህር በር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ
v የባህር በር ባለቤትነትና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት መብት ከዲፕሎማሲና ከዓለም አቀፍ ህጎች አንጻር
v የባህር በር ባለቤትነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር የሚዲያዎች ሚና የሚሉ ሲሆን በውይይት መድረኩ ላይ የመወያያ ጽሁፎቻቸውን ያቀረቡት
1ኛ) አቶ በቃሉ ዋቺሶ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ
2ኛ) አቶ እንዳለ ንጉሴ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ
3ኛ) ዶክተር አብድላዚዝ ዲኖ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ሲሆኑ በዚህ ወቅታዊና ሀገራዊ በሆነው አጀንዳ ላይ ምሁራዊ ትንታኔ አቅርበዋል፡፡
በጽሁፍ አቅራቢዎቹ በስፋት እንደተገለጸው ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ካላት የጂኦ- ፖለቲካዊ አቀማመጥ፣ በየጊዜው እያሳየች ካለቸው የኢኮኖሚ አቅም ዕድገት እና ካላት የህዝብ ብዛት አንጻር በቀጠናው አዎንታዊ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው በአንጻሩ ግን ወደብ አልባ ሀገር ከመሆኗ የተነሳ የወደብ ባለቤት በሆኑ የጎረቤት ሀገራት ላይ ጥገኛ በመሆን ወደ ውጭ ለምትልካቸው ምርቶችም ሆነ ወደ ሀገር ውስጥ ለምታስገባቸው ሸቀጦች ለወደብ ኪራይ ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ ላይ የምትገኝ በመሆኗ ይህ ሂደት በኢኮኖሚ አቅሟ ላይ ግዙፍ ሊባል የሚችል አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረባት እንደሚገኝ የጽሁፍ አቅራቢዎቹ አብራርተው ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያቀረበች ያለቸው የወደብ ተጠቃሚነት ጥያቄ ተገቢነትና ህጋዊ መሰረት ያለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጽሁፍ አቅራቢዎቹ ባቀረቡት የመወያያ መነሻ ጽሑፍ ላይ ከተሳታፊዎች ልዩ ልዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት