የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና ሆስፒታልን ጨምሮ እየሰጠ ያለውን ማህበረሰቡን ያማከለ አገልግሎት ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ከትምህርት ሚኒስቴር የመጣው የሱፐርቪዢን ቡድን አሳስቧል።
የሱፐርቪዢን ቡድኑ ማሳሰቢያውን የሰጠው ሰሞኑን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከቀን 21/02/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ባካሄደው የመስክ ምልከታ ማጠቃለያ ላይ በሰጠው ግብረ-መልስ ነው፡፡
የሱፐርቪዢን ቡድኑ በምልከታው የዩኒቨርሲቲውን ቤተሙከራዎች ፣ዲጂታል ቤተ-መፅሐፍት፣ የተማሪዎችን ማደሪያ፣ ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ፣ ዘመናዊ የዳቦ መጋገሪያ ፣የመመገቢያ አዳራሾችን፣ የህጻናት ማቆያን፣ ስማርት የሆኑ የመማሪያ ክፍሎችን፣ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያን፣ የዳልጋ ከብቶች ምርምርና እርባታን፣ የፈረዝዬን የምርምር ጣቢያን ፣የወልቂጤ ዩኒቨርሰቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን፣በግንባታ ላይ የሚገኘውን የአስተዳደር ህንጻ፣ የማዕከላዊ ቤተ ሙከራ እና የአይሲቲ ኮምፕሌክስ ህንጻ ፕሮጀክቶችን ጎብኝቷል፡፡
የሱፐርቪዢን ቡድኑ በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያም የተማሪዎች ህብረት አመራሮችንና እና ተማሪዎችን ፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞችን እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮችንም አወያይቷል፡፡
ከምልከታው መልስ የሱፐርቪዢን ቡድኑ ለዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ግብረ-መልስ ያቀረበ ሲሆን በግብረ መልሱም ዩኒቨርሲቲው በመውጫ ፈተና ያስመዘገበው ውጤት እጅግ አበረታች መሆኑን፣ መምህራን በምርምር ስራ ተሳትፎ የሚያደርጉበት Institutional Research Information Management System ( IRIMS ) ሶፍትዌር ተግባራዊ መደረጉን፣በግቢው ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መኖሩን፣ የተደራጀ የቴክኖሎጂ ቤተ-ሙከራና ማሽኖች መኖራቸውና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲጠቀሙበት ዕድል መሰጠቱን፣ ለመማሪያነት የሚያገለግሉ ስማርት ክፍሎች እና ዲጂታል ቤተ-መጽሐፍት መኖራቸውን፣ በተማሪዎች ምግብ ቤት አካባቢ ያለው አሰራር በእጅጉ የሚበረታታ መሆኑን፣ የዋቤ አግሮ ኢንደስትሪ ጅምር ስራ እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን፣ ለመምህራን አቅም በፈቀደ መጠን የመኖሪያ ቤት መመቻቸቱን፣ግቢው ንጹህና አረንጓዴ መሆኑ እና የህጻናት ማቆያ ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ በጠንካራ አፈጻጸም አንስቷል፡፡
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በመውጫ ፈተና ላይ ይበልጥ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባው፣ የዋቤ አግሮ ኢንደስትሪ ኢንተርፕራይዝን በሚገባ በማጠናከር በተለይም የወቅቱን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም እንዲረዳ የሰራተኛውን ኑሮ ማረጋጋት በሚችሉ ስራዎች ላይ በስፋት መሰራት እንዳለበት፣ በኢንተርፕራይዙ እየተመረተ ያለው የእንስሳት መኖ ምርት ወደ ማህበረሰቡ ተደራሽ በሚሆንበት መንገድ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የሱፐርቪዢን ቡድኑ አሳስቧል፡፡
በመጨረሻም የተማሪዎች ቀለብ በጀትና የመምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ሀገራዊና የሚታወቅ በመሆኑ መንግስት በጥናት ምላሽ እንዲሰጥበት ጉዳዩን ለትምህርት ሚኒስቴር እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የሱፐርቪዥን ቡድኑ የሰጠውን ግብረ መልስ በግብአትነት በመውሰድ የተሻለ ስራ እንደሚሰራ ያለውን የጸና እምነት ገልጿል፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት