በስልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብቴ ዱላ ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልጽግና የሚጫወተው ሚና ላቅ ያለ መሆኑን ጠቅሰው በአጠቃላይ ትምህርት ተደራሽነት ላይ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ቢሰሩም በዚህ ትይዩ ለጥራት የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ እንደሀገር የትምህርት ጥራት ስብራት እንዳጋጠመን አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የገጠመንን ችግር በዘላቂነት ለመሻገር በትምህርት ጥራት እና በምንሰጣቸው ፕሮግራሞች ተገቢነት ላይ ሰፊ ትኩረት ሰጥተን መስራታችን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ሀብቴ አያይዘውም የትምህርት ጥራት ሁለንተናዊ ትኩረቱ ተማሪዎችን በማህበራዊ፣ አእምራዊ፣ አካላዊና የእውቀት ዘርፎች ምክንያታዊ ዜጋ እንዲሆኑ ማስቻል በመሆኑ ጥራት ባለው ትምህርት የተማረ ሰው ሙሉ ስብዕናው ስለሚቀረጽ ራሱን፣ አከባቢዉን፣ ማህበረሰቡንና አገሩን እንደሚጠቅም ከግምት በማስገባት ለዚህም ትግበራ ፕሮግራሙ ሀገራዊና አለም አቀፋዊ መመዘኛዎችን ማሟላት እንደሚጠበቅበትም አጽንኦት በመስጠት ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በአካዳሚክ ፕሮግራም የሚሰጡት ትምህርቶች ሀገራዊና አለም አቀፋዊ መመዘኛ አሟልተው እውቅና (Accreditation) እንዲያገኙ በማድረግ ምሩቃን በስራ ገበያው የሚኖራቸው ተፈላጊነት ማሻሻል ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው በማመን ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በበጀት ዓመቱ የፕሮግራሞች ኦዲትና እውቅና ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ በእቅድ ውስጥ በማካተት በተመሳሳይ ግንዛቤ ላይ ተመስርቶ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ያስችላቸው ዘንድ ይህንን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ለአካዳሚክ ዘርፍ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ሃላፊዎች፣ ለአስተዳደር ዘርፍ ስራ አስፈጻሚዎችና የየዘርፍ ሃላፊዎች መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ጥራት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት አማካይነት የተዘጋጀው ይህ ስልጠና ከኢፌዴሪ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በመጡት የዘርፉ ባለሙያዎች በአቶ አብዱረህማን ያሲንና አቶ ተረፈ በላይ በመሰጠት ላይ ሲሆን ከህዳር 27- 28 ለሁለት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ከወጣው የጊዜ ሰሌዳ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ቢሮ