በመስክ ምልከታው ላይ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ ገብሩ፣ የክልሉ ማዕድን ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አጸደ አይዛ፣ የጉራጌ ዞን ዉሃና ማዕድን ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍሰሀ ዳምጠውን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል።
ከመስክ ምልከታው በኋላ በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ ገብሩ እንደገለጹት ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት አስር ዓመታት ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን በርካታ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው በተለይም በዘንድሮው ዓመት በባዮ ጋዝ ምርት ፣በጤፍና በቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት እንዲሁም ከክልሉና ከዞኑ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮዎች ጋር በጋራ በመቀናጀት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዶክተር ዮሀንስ አያይዘውም የቴክኖሎጂውን አስፈላጊነት በመረዳት ዩኒቨርሲቲው አርሶ አደሮችን የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለውን ውስን ሀብት አዋጪና ውጤታማ በሆነ ስራ ላይ ማዋሉን ገልጸዋል ፡፡ ከዚህ ቀደም የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን ጠቀሜታ አስመልክቶ ተጠቃሚው ማህበረሰብ ድረስ በመውረድ አርሶአደሩን በማግኘትና በማነጋገር በአርሶ አደሩ ዘንድ ያለውን ፍላጎትና ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ያላቸውን ተነሳሽነት በማረጋገጥ ስራውን አጠናክረው ለማስቀጠል መቻላቸውንም ዶክተር ዮሀንስ በስፋት ገልጸዋል ፡፡
በቀጣይም የጉራጌ ዞን በተለያዩ የተፈጥሮ የማዕድን ሀብቶች የታደለ በመሆኑ እነዚህን የማዕድን ሀብቶች በአግባቡ በመለየት ጥቅም ላይ ለማዋል ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸው ይህንንም ገቢራዊ ለማድረግ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጂኦ ፊዚክስ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ዩኒቨርሲቲው መፈራረሙን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አጸደ አይዛ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተደጋግፈው በመስራታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ተከናውኗል፡፡