ወልቂጤ ዩኒሽርሲቲ ከአትነት የጉራጊኛ ሙዚቀኞች ማህበር ጋር በጉራጊኛ ሙዚቃ ልማት ዙርያ በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ። ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲን በመወከል የመግባቢያ ስምምነቱን የፈረሙት የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ዮሀንስ ገብሩ ሲሆኑ እሳቸውም ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት እንደገለጹት የጉራጊኛ ቋንቋ ፣ ባህል እና ሀገር-በቀል ዕውቀቶች እንዲለሙ ብሎም ለትውልድ እንዲተላለፉ ሙዚቃ ያለዉ ድርሻ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ሙያው ምርምርና ሳይንሳዊ ድጋፍ እንደሚሻም አስገንዘበዋል። አትነት የጉራጊኛ ሙዚቀኞች ማህበርን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት አቶ አምደሚካኤል አድማሱ በበኩላቸው ስምምነቱ ቴክኒካዊ ድጋፍ የሚያስገኝ ስለሆነ የጉራጊኛ ቋንቋ አርቲስቶች ህብረት እንዲጠናከር ያግዛል ብለዋል። ስምምነቱ በምርምር ፣ በስልጠና፣ በሙያዊ ክህሎት ልውውጥ እና በቁሳዊ ድጋፎች አቅርቦት ላይ በትብብር መስራትን ያካትታል።