“ ሀገራዊ መግባባት ለብሄራዊ አንድነት በሚል መሪ ቃል “19ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በደማቅ ስነስርዓት ተከብሮ ውሏል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዘሀ ብሄሮች መገኛ እና መድመቂያ እንደመሆኗ መጠን ዕለቱን ስናከብር የህብረ ብሄራዊ ቀለማት ድምቀት መሆናችንን በማሳየት ጭምር መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም ይህ የዳበረና በህዝቦች የአብሮነት መስተጋብር የደመቀው ብሄራዊነት ለላቀ የሀገር ግንባታ መዋል እንዳለበት ገልጸው ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አጽንኦት በመስጠት አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም የሀገራችን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወሰነው ዛሬ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እያስተማሩ ባሉ ምሁራንና ተማሪዎች ስለሆነ ምሁራን ለዚህ ተግባር ምሁራዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት ሀገርን የማሻገር ሚናቸውን እንዲወጡ ተማሪዎችም እንደሀገር ተረካቢነታቸው ጠንክረው በመማር ውጤታማነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ዶክተር ፋሪስ ገልጸዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ “ህብረ ብሄራዊ ፌደራል ስርዓት በኢትዮጵያ ፤ የፌደራላዊ እሳቤ አስፈላጊነት” የሚል ጥናታዊ ጽሁፍ በመምህር በቃሉ ዋቺሶ እንዲሁም "የህብረ ብሄራዊ ፌደራል ስርዓት ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ እና የመፍትሄ ሃሳቦች “ በሚል ርእስ በመምህር አብዱልከሪም ሻፊ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ፕሮግራሙ በአባቶች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን በመድረኩ ላይ ለታዳሚዎች ልዩ ልዩ የስነጽሁፍ ስራዎች ቀርበዋል ፡፡
ለጥበብ እንተጋለን!
We Strive for Wisdom!
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት