በወልቂጤ ከተማ በሚገኘው በባሮክ ሆቴል ሲሰጥ የቆየው ይህ ስልጠና በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት በክብርት ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ተነሳሽነት የዩኒቨርሲቲው የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ከአለም አቀፍ የትምህርት ተቋም /Institute of International Education/ ከተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በጋራ በመተባበር ያዘጋጁት ስልጠና ሲሆን ስልጠናው ላለፉት አራት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ ቆይቶ በትናንትናው ዕለት በይፋ ተጠናቅቋል፡፡ ስልጠናውን የተካፈሉት ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ 40 ሴት መምህራን ሲሆኑ ሴት መምህራኑ በወሰዱት ስልጠና መሰረት እያንዳንዳቸው 5 ሴት ተማሪዎችን በመያዝ በቀጣይ 200 ሴት ተማሪዎችን እንደሚያሰለጥኑ ሥልጠናውን ያዘጋጁት አካላት ገልጸዋል ፡፡
በስልጠናው መዝጊያ ላይ ለሰልጣኞቹ የምስክር ወረቀት የሰጡት ዶክተር የሻረግ አፈራ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ኮርፖሬት ማኔጅመንት ምክትል ፕሬዝዳንት እና ወ/ሮ መሰረት አስራት የዩኒቨርስቲው የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ሲሆኑ ለስልጠናው ፍሬያማነት የሴት መምህራኖቹ ሚና እጅግ ጉልህ መሆኑን በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገልጿል፡፡