አዲስ ማለዳ መስከረም 14/2015 ዓም በቅጽ 4 በቁጥር 203 እትሙ ላይ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲን አስመልክቶ ካወጣው ዘገባ ጋር በተያያዘ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተገቢውን የሆነ የማጣራት ስራ ለማድረግ እንዲረዳው አጣሪ ኮሚቴ በማዋቀር የማጣራት ስራውን ጀምሯል፡፡
በዚህም መሰረት መስከረም 16/2015 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ በስሩ ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ አባላት ያሉት ኮሚቴ ተዋቅሮ በ18/01/2015 ዓ.ም ስራውን ሲያጣራ ውሏል፡፡
የተዋቀረው ኮሚቴም የማጣራት ስራውን ካገኘው ጥቆማ መነሻ ከ2014 ዓም የዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች የጀመረ ሲሆን በማጣራት ስራው ሂደት ላይ ከዩኒቨርሲቲው Student Information Management System (SIMS) የመረጃ ቋት ላይ በሁሉም ኮሌጆች በመደበኛው፣ በሳምንት መጨረሻ፣በክረምትና በማታው የትምህርት መርሃ-ግብር የተመረቁትን ተማሪዎች መረጃ ከመረጃ ቋቱ ላይ በማውረድ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ካጸደቀው የተመራቂዎች ዝርዝር ቃለ-ጉባኤ ጋር የማነጻጸር ሥራ ሰርቷል፡፡
በዚህም መሰረት አዲስ ማለዳ ባወጣው ጋዜጣ የገለፀው እና ምክትል ዋና አዘጋጇ ወ/ሪት ሊዲያ ተስፋዬ በ18/01/2015 ዓ.ም ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል የሠጡት መረጃ መነሻ ተደርጎ ማጣራቱ ተጀምሯል፡፡ ምንም እንኳ ምክትል አዘጋጇ በ18/01/2015 ዓ.ም በስልክ በሰጡት መረጃ ‹‹የ2014 ዓም በማኔጅመንት የትምህርት ክፍል የተመረቁትን አጣሩ›› ያሉ ቢሆንም ባለፉት አራት አመታት በሀገራችን የስርዓተ-ትምህርት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ በ2014ዓ.ም በመደበኛው መርሃ-ግብር በማኔጅመንት ፕሮግራም የተመረቁ ተመራቂዎች አለመኖራቸውን ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡ በአንጻሩ አዲስ ማለዳ ‹‹ ሁለት ወራት አጣርቼ አረጋግጫለሁ” ብሎ ያወጣው ዘገባ እውነት ስለመሆኑ አንድም ፍንጭ አልተገኘም፡፡
ለማሳያም በዩኒቨርሲቲያችን ህግና አሰራር መሰረት የተማሪዎች ምረቃ የሚረጋገጠው በዩኒቨርሲቲው ሴኔት የመጨረሻ ውሳኔ ሲሆን ይህም የሚከናወነው አስቀድሞ ከየትምህርት ክፍሎች ተገቢው የተመራቂዎች መረጃ ተጠናቅሮና ጸድቆ ወደ በኮሌጆች አካዳሚክ ኮሚሽን ከተረጋገጠ እና ከጸደቀ በኋላ ወደ ዋናው ሬጅስትራር የሚላከው የእጩ ተመራቂዎች ዝርዝር በሴኔት ከጸደቀ በኋላ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በ2014 ዓም የትምህርት ዘመን የተመረቁ ተማሪዎችን በተመለከተ በአጣሪው ኮሚቴ የማጣራት ሂደቱ ወቅት አንድም የተፋለሰ መረጃ አልተገኘም፡፡