የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት፣ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አባላት ፣ የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት መምሪያ አባላት እና የጉራጌ ዞን ጸጥታ ዘርፍ በዛሬው ዕለት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በጋራ በመገናኘት የ2015 ዓም የ12ኛ ክፍል ፈተና ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ሰፊ የሆነ የጋራ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የቅድመ ዝግጅቱን ሁኔታ አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት ከዚህ ቀደም ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት ዝግጅቱን መገምገማቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል ገልጸዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን ዝግጅት አስመልክቶ ዶክተር ፋሪስ ደሊል ሲገልጹ በአካዳሚክ ዘርፍ የመፈተኛ ክፍሎችንና የተለያዩ ግብዓቶችን በማሟላት እንዲሁም በአስተዳደር ዘርፍ የምግብ ፣ የመኝታና የህክምና አገልግሎቶችን በማሟላት ረገድ ዝርዝር ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው ያሉትን ክፍተቶችን በመለየት ለቀጣይ ተገቢው ርብርብ ተደርጎ ተገቢው የእርምት ርምጃ መውሰድ እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
በዞኑ በኩል በትራንስፖርት አቅርቦት ረገድ የተደረገውን ዝግጅትና የተፈታኝ ተማሪዎችን ስም ዝርዝርና መለያ ቁጥር አስቀድሞ በመለየት ለዩኒቨርሲቲው መቅረብ እንደሚገባው ተገልጿል፡፡ የጸጥታም ሁኔታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንደሚገባውም በውይይቱ ላይ ተብራርቷል፡፡
ተማሪዎች በፈተናው ዕለት እንዳይረበሹና ከመኖሪያ ስፍራቸውም ሲንቀሳቀሱ መንጠባጠብ ሳይኖር በተቀናጀ ሁኔታ ለማስኬድ እንዲረዳ በወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት በኩል ለርዕሣነ መምህራን ገለጻ ቢሰጥና በተመሳሳይም ርዕሳነ መምህራንም ተማሪዎችን በማሰባሰብ ተገቢውን ገለጻ እንዲሰጡ ለመግባባት ተችሏል፡፡
ወደ ዩኒቨርሲቲው የማድረጊያ ጊዜ ራቅ ያሉ አካባቢዎች ከመስከረም 26 የሚጀምር ሆኖ የተቀሩት መስከረም 27 እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ለሚዘገዩት እና በዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ላሉት መስከረም 28/2015 የመጨረሻው ቀን እንደሚሆን ተብራርቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የየወረዳዎቹና የየትምህርት ቤቶች የፈተና አስተባበሪዎች ተፈታኝ ተማሪዎችን እስከ ዩኒቨርሲቲው ድረስ አምጥተው የሚያሰረክቡበት መንገድ እንዲመቻች በሚል የውይይቱ ተሳታፊዎች በጋራ ተስማምተዋል፡፡
በመጨረሻም ተማሪዎቹ ወደ ተቋሙ ሲመጡ ይዘው መምጣት የተከለከሉ እና የተፈቀዱ ነገሮች አስመልክቶ በየትምህርት ቤቱ አማካይነት በሚደረግላቸው ገለጻ ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ቢሰራ ወደዩኒቨርሲቲው ከመጡ በኋላ ተማሪዎቹ ላይ ሊፈጠር የሚችል እንግልት እንደማይኖር ተገልጿል፡፡
ከውይይቱ በኋላ የተደረገውን አጠቃላይ ዝግጅት አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት፣ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አባላት ፣ የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት መምሪያ አባላት እና የጉራጌ ዞን ጸጥታ ዘርፍ ተዟዙረው ጎብኝተዋል፡፡