ጳጉሜ 1/2014 ዓም የበጎ ፈቃድ ቀንን ምክንያት በማድረግ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት አባላት በወልቂጤ ከተማ ልዩ መጠሪያው እነሞር ሰፈር በሚባለው ስፍራ በመገኘት ሙሉ ወጪው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተሸፍኖ እየተገነባ ያለውን የወ/ሮ ሰኒያ መሀመድ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ያለበትን ደረጃ ጎበኙ፡፡
የወ/ሮ ሰኒያ መሀመድ የመኖሪያ ቤትን ከዚህ ቀደም የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ደኤታ የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት አባላት ጋር በጋራ በመሆን የማደስ ስራውን ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው፡፡
በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት የጣሪያና የግድግዳ ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች መቅረባቸውን የማኔጅመንት አባላቱ በማረጋገጥ ግንባታውን በቅርበት እየተከታተሉ ካሉት የከተማው አስተዳደር አካላት ጋር በመገናኘት ቀሪ ስራዎች በፍጥነት ተጠናቅቀው ግለሰቧን ወደ አዲሱ የመኖሪያ ቤታቸው ለማስገባት ጥረት እንዲደረግና ለቀሪ ስራዎቹም ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የማኔጅመንት አባላቱ አረጋግጠዋል፡፡
የቤት እደሳቱ የተከናወነላቸው ወ/ሮ ሰኒያ መሀመድ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ቤቱ ከዚህ ቀደም በጣም ያፈስባቸው እንደነበርና በተለይም ክረምት በመጣ ወቅት በጎርፍ ይጠቁ እንደነበር ገልጸው የሶስት ልጆች እናት በመሆናቸው ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ልብስ በማጠብና እንጀራ በመጋገር ስራ ላይ መሰማራታቸውን በማስታወስ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እጅግ ከባድ በሆነ የፈተና ወቅት ላይ ደርሶ ላደረገላቸው እገዛ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተመሳሳይ ሌሎች የቤት እድሳት ድጋፍ የተደረገላቸው አካላትን ያሉባቸውን ክፍተቶች በመለየት በአስቸኳይ መፍትሄ ለመስጠት በመስራት ላይ እንደሚገኝ የማኔጅመንት አባላቱ ገልጸዋል፡፡