በ2014 የትምህርት ዘመን በትምህርት ሚኒስቴር ተመድበው በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የተመደቡ 4201 ተማሪዎች ወደተቋማችን መመደባቸውና ከግንቦት 03/2014 ጀምሮ የአቀባበል ስነስርዓት ሲደረግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በዛሬው ዕለት ባለፉት የቅበላ ቀናት ወደ ዩኒቨርሲቲያችን ለመጡትና ለተቀበልናቸው ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትና በዩኒቨርሲቲው መተዳደሪያ ደንቦች እና የስነ ምግባር መርህዎች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ተሰጥቷል።
ፕሮግራሙ በሀገር ሽማግሌዎች የምርቃት ስነስርዓት የተጀመረ ሲሆን በመድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል እንደገለጹት የሠላም ተምሳሌት ፤የአብሮነት መገለጫ፤ የፍቅር አብነት ወደ ሆነው በታታሪውና በስራ ወዳዱ ማህበረሰብ ዙሪያውን ታጅቦ ወደሚገኘው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እንኳን በሠላም መጣችሁ በማለት ንግግራቸውን ጀምረዋል ። በተጨማሪም ዶክተር ፋሪስ በመልዕክታቸው ላይ እንደገለጹት “ምንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይታችሁ ብንቀበላችሁም ከትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠን ተልዕኮ መሰረት እናንተን በእውቀት በማበልጸግ፤በክህሎት በማዳበርና በአስተሳሰብ በማጎልመስ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ሆናችሁ ሀገራችን በምትፈልጋችሁ ልክ እንድትመረቁ ለማድረግ የሚጠበቅብንን ሁለንተናዊ ሃላፊነት ለመወጣት ያለንን ዝግጁነት ከወዲሁ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ’’ በማለት መልዕታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ዶክተር ፋሪስ አያይዘውም የቀድሞ ልምዶቻችን እንደሚያስተምሩን ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ይፈተናሉ:: ለምሳሌ በግል ህይወታቸው ደረጃ በሚገጥማቸው ልዩ ልዩ ሁኔታዎች፣ በተለያዩ ውዥንብሮች፣ ዓላማቸውን በሚያስተጓጉሉ ደንቃራ ሁኔታዎችና የራሳቸውን የፖለቲካ አመለካከት ሊጭኑባቸው በሚፈልጉ ሴረኞች እንደሚፈተኑ አስታውሰው ነገር ግን ለሚገጥማቸው ማናቸውም ፈተና ሳይበገሩ በጽናት እንዲወጡ ጭምር አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የተማሪዎች የዲሲፕሊን አፈጻጸም መመሪያ፤ ስለ አካዳሚክ ህግና ደንቦች ፤ሰለቤተመጻህፍት አጠቃቀም አስመልክቶ ያሉትን ህግና ደንቦችና እንዲሁም ስለ ተማሪዎች ህብረት በተመለከተ ሰፊ ገለጻ ተደርጓል፡፡