• Registration

 

ዩኒቨርሲቲው በተቋሙና በጉራጌ ዞን ከሚገኙት የመስኩ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች  ጋር ለመወያየት ባዘጋጀው የፕሮጀክቱ ማስተዋወቂያ መድረክ ታዋቂው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሀ ፖለቲካ ሳይንስ  መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አሳኖ ተገኝተው ምክረ-ሀሳባቸውን አቀረቡ፡፡

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ሲሳይ ሸዋአማረ እንደተናገሩት የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ የጠፉትን ወንዞችና እርጥበታማ መሬቶችን በመመለስና በመጥፋት ላይ የሚገኙትን በመንከባከብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑን አመልክተው ፕሮጀክቱ ተጠናክሮ ሲቀጥልም ዩኒቨርሲቲው በመስኩ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት የሚያስችል የድህረ ምረቃ ትምህርት ፐሮግራም ለመክፈት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡ ከውይይቱ የሚቀርቡ ምክረ-ሀሳቦችም የፕሮጀክቱን ዓላማ ለማሳካት አጋዥ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡

በምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት የኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበበ ያበኬር በበኩላቸውየማስተዋወቂያ መድረኩ አስፈላጊነት በአሁኑ ወቅት እጅግ አስጊ እየሆነ የመጣውን የወንዞችና የእርጥበታማ መሬቶች የመጥፋት ችግር ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የሚሆኑበት የተቀናጀ አሰራር ለመፍጠር እንደሆነ ገልጸው ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ውይይት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

በዚሁ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሀ ፖለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ በሆኑት በፕሮፌሰር ያዕቆብ አሳኖና በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የሀይድሮሊክስና አንቫይሮመንት ትምህርት ክፍል መምህር በሆኑት በአቶ አለሙ በየነ አማካይነት በዞኑ የጠፉ ወንዞችና እርጥበታማ መሬቶችን ለመመለስ በሚያስችልሁኔታ ላይ ትኩረት በማድረግ የተዘጋጁ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ እነዚህ ጽሑፎች መነሻ በማድረግም  ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

 ጥናቶቹ እንዳመለከቱት የጉራጌ ዞን በአገራችን የውሀ ማማ ከሚባሉት አካባቢዎች መካከል አንዱ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የሚደርቁና የውሀ ፍሰታቸውን የሚቀንሱ ወንዞች ቁጥር እያሻቀበ መጥቷል፡፡ በርካታ ምንጮችም በተመሳሳይ ሁኔታ እየደረቁ ከፊሎቹም ውሀ የማመንጨት አቅም እያጠራቸው ነው፡፡ እንዲሁም እርጥበታማ ቦታዎች በመጥፋት ላይ የሚገኙ ሲሆን ውሀን በቁፋሮ ለማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በሆነ  ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ለእነዚህ ችግሮች መንስኤ ከሆኑት መካከል ውሀን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያስችል ሥርዓት አለመዘርጋትና የአየር ንብረትለውጥ ዋነኛ ተጠቃሽ መንስኤዎች መሆናቸውን ተጠቅሷል፡፡ በየጊዜው እያደገ የመጣው የህዝብ ብዛት፣ የተዛባ የውሀ አጠቃቀምና ውሀን እንደ ሀብት ቆጥሮ አለመጠበቅና አለመንከባከብ ችግሩን የሚያቀጣጥሉ ተያያዥነት ያላቸው መንስኤዎች መሆናቸውን ምሁራኑ ገልጸዋል፡፡ በየአካባቢው እየተስፋፋ የመጣው የባህር ዛፍ ተከላም ችግሩን እያባባሰው መሆኑን ገልጸው እንደ ቀርከሀ በመሳሰሉ ለአካባቢ ተስማሚና ሁለንተናዊ ጥቅም ባላቸው ዛፊች መተካት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ሽፋን ያለው ቢሆንም በጉራጌ ዞን ያለው ሁኔታ የከፋ መሆኑን በውይይቱ የተሳተፉት ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች አመልክተው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ዘግይቶም ቢሆን በዚህ የማህበረሰቡን ሥጋት በሆነ ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገ እንቅስቃሴ በመጀመሩ አመስግነዋል፡፡ ፈጥኖ ወደ ተግባር መግባት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ፕሮፌሰር ያዕቆብ በበኩላቸው በተለያዩ አገሮች በታየው ልምድ መሰረት የደረቁና የውሀ ፍሰታቸው የቀነሱ ወንዞች ወደነበሩበት መመለስ አንደሚቻል ገልጸው ሆኖም በዚህ ሂደት የሶስቱ ባለድርሻ አካላት ማለትም የመንግስት፣ የማህበረሰቡና የዩኒቨርሲቲው የተቀናጀ እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሰረት የጉራጌ ዞን መንግስት የተለያዩ ፖሊሲዎች፤ ደንቦችና መመሪያዎች አውጥቶ  ለማህበረሰቡ በማስተዋወቅና በማስተባበር፣ ማህበረሰቡም በጉዳዩ የባለቤትነት ስሜት ፈጥሮ በመንቀሳቀስና ዩኒቨርሲቲው ደግሞ በጥናትና ምርምር ሥራ የተደገፈ ሳይንሳዊ ዕውቀት በማቅረብ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሌሎች የሚመለከታቸው ግብረሰናይ ድርጅቶችም ከነዚሁ ወገኖች ጋር ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ሥራውም  አጠቃላይ በዞኑ የሚገኙት ወንዞች ብዛት፣ ከነዚህ ውስጥ የደረቁትንና በመድረቅ ላይ የሚገኙትን ወንዞችና ምንጮች ቁጥር መንስኤዎቻቸውም ጭምር በማጥናት መጀመር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዞኑ የውሀ፣ ማዕድንና አነርጂ መምሪያ የበላይ ኃላፊዎችና የመስኩ ባለሙያዎች ችግሩን በመከላከል ላይ ያተኮሩ በርካታ ሥራዎች መኖራቸው ገልጸው ነገር ግን አሁን በዩኒቨርሲቲው በታሰበው መልኩ የተቀናጀ አሰራር ባለመኖሩ ከታሰበው ውጤት ላይ መድረስ አልተቻለም ብለዋል፡፡ ስለሆነም አሁን በዩኒቨርሲቲው የተጀመረው አንቅስቃሴ ለዞኑ ትልቅ ዕድል የሚሰጥና በዞኑ መንግስት ዓላማላይ የተመሰረተ በመሆኑ ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡ የዞኑ ማህበረሰብም ችግሩን በሚገባ የተገነዘበው ስለሆነ የፕሮጀክቱን ዓላማ እንዲያውቀው ከተደረገ ባህላዊ ዕውቀቱንም ተጠቅሞ የበኩሉን ኃላፊን በመወጣት ረገድ ችግር የሌለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል እንደተናገሩት ከዚህ የማስተዋወቂያ መድረክ የተገኘውን ግብአት በመጠቀም አስፈላጊውን ዝግጅት ተደርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፕሮጀክቱ ወሳኝ ባለድርሻ አካላት የሆኑት የዞኑ መንግስት፣ የማህበረሰቡ ተወካዮችና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ተባባሪ አካላት በዞኑ ባለውና በቀጣይ ሊያጋጥም በሚችለው የውሀ ሀብት ችግር ላይ በጋራ መክሮ የጋራ መፍትሄ ለማስቀመጥ የሚያስችል የጋራ መድረክ ይዘጋጃል፡፡ ዝርዝር ጥናት ተደርጎም ችግሩን በቅደም-ተከተል በማስቀመጥ ሥራውን የከፋ ችግር ካለበት  ይጀመርና ከእሱም በሚገኘው ልምድ ወደ ሌሎቹ እየሰፋ የሚሄድበት የአሰራር ሥርዓት ተከትሎ ተፈጻሚ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በአዲስ አበባ የውሀ ፖለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ አንዲሁም በወቅቱ የግብፅ መንግስት የሕዳሴው ግድብን አስመልክቶ ባስከፈተው አጀንዳ  ላይ አትዮጵያን ወክለው የሚደራደሩና በማናቸውም የውሀ ጉዳዮች ዙሪያ መንግስትን በማማከር ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አሳኖ አጠቃላይ የፕሮጀክቱን የአፈጻጸም ሂደት በማማከር ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር አብረው በመሥራት አንደሚቆዩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

Copyright © 2020. Wolkite University. Designed by Wolkite University ICT

Login Form

Register